አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ፤ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም – የቢሊ ግራሃም የወንጌል ማኅበር በ1952 ዓ.ም ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም በአዲስ አበባ ስቴዲየም ወንጌል ከሰበኩና በንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ በቤተ መንግስታቸው በክብር ተጋብዘው ከተሸለሙ ከ65 ዓመታት በኋላ የካቲት 29 እና 30 በመስቀል አደባባይ በሚደረገው ታሪካዊ የሁለት ቀናት መርሐ ግብር ላይ ለማገልገል ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አማካኝነት በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ1,600 በላይ የሚሆኑ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፤ የወንጌላዊ ቢሊ ግርሃም ልጅ ሬቨረንድ ፍራንክሊን ግርሃም በአዲስ አበባ ተገኝተው የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል እንዲሰብኩ በመጋበዝ ለዝግጅቱ መሳካት ከቢሊ ግራሃም የወንጌል ማኅበር /ቢሊግርሃም ኢቫንጀሊስቲክ አሶሴሽን/ ጋር በመተባበር በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ልክ እንደ አባታቸው ፍራንክሊን ግራሃም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥልቅ እና ታላቅ አክብሮት ያላቸው ስለሆነ ባለፉት 40 አመታት ወደዚህች ሀገር በተደጋጋሚ መጥተዋል።
“ኢትዮጵያ ውብና ጠንካራ አገር ነች። ከዚህ ታላቅ አገር ህዝብ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሁል ጊዜ እጓጓለሁ ”ሲሉ የቢሊ ግርሃም ኢቫንጀሊስቲክ አሶሴሽን (BGEA) ፕሬዝዳንት እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለአስርት ዓመታት በበጎ አድራጎት ሥራ ተሰማርቶ ሲሠራ የቆየው የአለም አቀፍ የክርስቲያን ዕርዳታ ድርጅት የሆነው የሳማሪታን ፐርስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሬቨረንድ ፍራንክሊን ግራሃም ተናግረዋል። “አገሪቷን ስጎበኝ ይህ ለ11ኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጉዞየ ግን ከዚህ ቀደም ሠርቼው የማላውቀው አዲስ ነገር እንደሚሆን አምናለሁ። በአብያተ ክርስቲያናት ግብዣ በአገሪቱ ትልቁ አደባባይ በመገኘት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሆን መልእክት አቀርባለሁ። እሱም ሕይወት ለዋጭ የሆነው እግዚአብሔር እንደሚወደን፣ እንደሚንከባከበንና ለሕይወታችን ዓላማ እንዳለው የሚያሳይ የምሥራች መልዕክት ነው።”
የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጉብኝት ደስታ በዋና ከተማው እና በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ሕይወታቸውን እየገነባ እንዳለ ይታያል። በዚህ ዝግጅት ላይ ለወንጌል መልዕክት ምላሽ የሚሰጡትን ጨምሮ፥ አማኞች የክርስቶስን ፍቅር ከሌሎች ጋር በብቃት እንዲካፈሉ ለማገዝ በቢሊ ግራሃም ኢቫንጀሊስቲክ አሶሴሽን የስልጠና ክፍለ ጊዜዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአጥቢያ ቤተክርስቲያን አባላት ተሳትፈዋል። በዝግጅቱ ላይ የመጓጓዣ ትራንስፖርት በማጣት ለመሳተፍ የሚቸገሩ ሰዎችን ወደ መለኮታዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ መርሐ ግብር ለማምጣት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነጻ አውቶቡሶች ለስምሪት ተዘጋጅተዋል። በከተማውና በዙሪያዋ በርካታ የጸሎት ቡድኖች በእያንዳንዱ ቀን ስለመርሐ ግብሩ የማያቋርጥ ጸሎት በመጸለይ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ፣ “ብዙ የተለያዩ ፈተናዎች እና ትግሎች አሉብን – ለዚህም ድህነት እና ግጭት የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። አሁን ጊዜው የተሐድሶና የመነቃቃት ወቅት ነው ብለን እናምናለን። ለዚህም የሚያስፈልገን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። በአሁኑ ወቅት ለምድራችን ፈውስ ሊያመጣ የሚችለው እና የሰዎችን ልብና አእምሮንም ሊለውጥ የሚቻለው ወንጌል ብቻ እንደሆነ እናምናለን።”በማለት ተናግረዋል። በማስከተልም፥ እንደቃሉ “ እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር እንዘረጋለን። እርሱን ስናዳምጥ የእያንዳንዳችን ሕይወት ይለውጣል፥ ሀገርም ትለወጣለች። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ፊት ለተሐድሶ እንፈልጋለን፥ በዚህች ምድር እግዚአብሔር የሚያደርገውንም ለማየት እጓጓለሁ፤ በአብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን በሀገራችንም ጭምር አዲስ ነገር ይሆን ዘንድ ፊቱን መፈለግ አለብን” ብለዋል።
መለኮታዊ ጉብኝት ሁሉም ሰው እንዲካፈለው የተጋበዘበት መርሐ ግብር ነው። የዝማሬ አገልግሎት ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ከአሜሪካን ሀገር በመጡ መዘምራንና በዛ ባሉ ኢትዮጵያዊያን የሶሎ መዘምራን ይቀርባል፣ ዘማሪ አቤኔዘር ለገሰ፥ መጋቢ አገኘሁ ይደግ፥ ዘማሪ ሃና ተክሌ፣ ዘማሪ ጉቱ ሽፈራውና የኅብረት መዘምራን ዝማሬ ያቀርባሉ።
ስለመለኮታዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ መረጃ ቢያስፈልግዎ እና በመርሐ ግብር ለመሳተፍ ቢያሻዎ እባክዎ https://EncounteringGod.BillyGraham.org/am/. የተሰኘውን ድረ ገጽ ይጎብኙ።
የሚዲያ ግንኙነት
ጥላሁን ጉግሳ መንገሻ፥ tilahungu.77@gmail.com, +251 91 120 4463
ለብዙሃን መገናኛ የተዘጋጀ መርሐ ግብር
• ሰኞ፥ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ቢሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ለተለያዩ የክርስቲያን ሚዲያ ባለሙያዎች ይሰጣሉ።
• አርብ፥ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 5 ሰዓት ላይ ሬቨረንድ ፍራንክሊን ግርሃም በሸራተን አዲስ ሆቴል መርሐ ግብሩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ለተለያዩ የሚዲያ አካላት ይሰጣሉ።
• ሁሉም ጋዜጠኞች የሁለቱን ቀናት መርሐ ግብር፥ የካቲት 29 እና 30 በመስቀል አደባባይ በመገኘት እንዲካፈሉ ተጋብዘዋል።
• ሬቨረንድ ግርሃምን ቃለ መጠይቅ ለማድረግና በመለኮታዊ ጉብኝት ለኢትዮጵያ መርሐ ግብር ለመካፈል አርቲስት ጥላሁን ጉግሳን ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በማግኘት የሚዲያ መመሪያና የመግቢያ ማረጋገጫ ማግኘት ይችላሉ።
• ፍራንክሊን ግርሃም በተለያዩ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላከናወኑት ክንውን እና ቢሊ ግርሃም ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር እንደነበሩ የሚያሳዩ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ፎቶግራፎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማውረድ https://Media.BillyGraham.org/Encountering-God-with-Franklin-Graham-Ethiopia-am/. ይጎብኙ።
ስለ ፍራንክሊን ግርሃም እና ስለ ቢሊግራሃም ኢቫንጀሊስቲክ አሶሴሽን
እ ኤ አ በ1950 በቢሊግርሃም የተመሰረተው የቢሊግራሃም ኢቫንጀሊስቲክ አሶሴሽን በዓለም ዙሪያ ወንጌልን በማሰራጨት ላይ ይገኛል። ፍራንክሊን ግርሃም የመጀመሪያ የወንጌል አገልግሎት ያደረጉት እ.ኤአ በ1989 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምስራቹን ወንጌል በ55 ሀገራት ከ325 በላይ የወንጌል ማሰራጫ ጣቢያዎች አድርገዋል። በቅርቡ፥ ሬቨረንድ ግርሃም የኢየሱስ ክርስቶስ ተስፋን በቪይንትያኔ – ላኦስ፥ በካን ታሆ- ቬትናም፥ በኔፕልስ- ጣሊያን፥ በቢርሚንግሃም – እንግሊዝ፥ በግላስጎ-ስኮትላንድ፥ በካራኮ – ፖላንድ፥ በሚክሲኮ ሲቲ – ሜክሲኮ፥ እና በአሜሪካና ሜክሲኮ ድንበሮች በሚገኙ 10 ከተሞች የምስራቹን ቃል ሰብከዋል። ከአዲስ አበባው አገልግሎት በኋላ በለንደን – እንግሊዝ፥ በብራስልስ – ቤልጂየም እና በቦነስ አየርስ – አርጀንቲና በዚህ በፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ ያደርጋሉ።
ስለ ሳማሪታን ፐርስ
ከቢሊግርሃም ኢቫንጀሊስቲክ አሶሴሽን ፕሬዚዳንትነትና ዋና ሥራ አስፈጻሚነት በተጨማሪ ፍራንክሊን ግርሃም፥ በዓለም ዙሪያ ከ100 በላይ በሆኑ ሀገራት ያሉ ስደተኞችን፥ የጦርነትና የተፈጥሮ አደጋ ተጎጂዎችን፥ ሕሙማንን፥ ድሆችን የሚረዳውን የዓለም አቀፉን የክርስቲያን ዕርዳታና የወንጌል ተቋም የሆነውን ሳማሪታን ፐርስን በኃላፊነት በመምራት ላይ ይገኛሉ። የሳምሪታን ፐርስ የዕርዳታ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ተቋም ነው። በእ.ኤአ ከ1988 ከፍተኛ የሆነ ድርቅና ረሃብ በሀገሪቱ በተከሰተበት ወቅት ድርጅቱ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር፥ የገጠር ግብርና ፕሮግራሞች በማዘጋጀት ድጋፍ አድርጓል። ፍራንክሊን ግርሃም ባለፉት ዓመታት እነኝህን ፕሮጄክቶች የሥራ እንቅስቃሴ ለመመልከትና የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መጋቢያንን ለመጎብኘት ወደ ሀገሪቱ መጥተዋል።
– 30 –
የፍራንክሊን ግርሃም የሚዲያ ግንኙነት
ማርክ ባርበር
mebarber@bgea.org